ሳታ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ ከተለያዩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ከሆኑ የመንግሥትና የግል እንዱስትሪዎችና ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ሥራ ስምምነቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝ አስታወቀ::

0 Comments

ሳታ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ በአከባቢውና በሀገር ደረጃ ከሚገኙ አምራችና አገልግሎት ሰጪ የመንግሥትና የግል እንዱስትሪዎችና ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ጥቅም በሚያስገኙ የሥራ ስምምነቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝ ገልጿል።

አቶ ባዩ ታየ የኮሌጁ እንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሲሆኑ በመንግስት የትምህርት ፖሊሲ በተሰጠው የትኩረት አቅጣጫና የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማትና እንዱስትሪ ትስስር ቁጥር 1298/2015 መሠረት አዋጅን ተከትሎ ስምምነቶችን በመፈፀም እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ኮሌጁ የሁለትዮሽ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ትሥሥር (University/college Industry Linkage) በመፍጠር መሥራትን በፅኑ እንደሚያምን የገለፁት አቶ ባዩ የዳይሬክቶሬቱን የአጭርና ረጅም ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት ኮሌጁ በዞኑ፣ በክልል፣ በአገር አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከኤምባሲዎች ጋር የእንዱስትሪ ትስስር በመፍጠርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ መሠረት የሚጥሉ የጋራ መግባቢያ ሠነዶችን (Memorandum of Understanding (MoU) ለመፈራም ቀደም ሲል የተፈረሙትንም ለማደስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንና አሁንም ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየተፈራረመ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አክለውም መጋቢት 30/2016 ዓ፣ም ከአንጋፋው ጋሞ ልማት ማህበር ጋር በቀጣይ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ታሪካዊ የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን ገልፀው በስምምነት ሠነዱ መሠረትም ኮሌጁ ለጋሞ ልማት ማህበር ሠራተኞችን በአይሲቲና በሂሳብ ሙያ ዘርፍ የአጭር ጊዜ ሥልጠና ለመስጠት፣ ከደሀ ደሀ ቤተሰብ በልማት ማህበሩ በኩል ተለይተው ለሚመጡ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ለመስጠት፣ለባይራ ሞዴል ትምህርት ቤት የመማሪያ መጽሀፍት ድጋፍ ለማድረግና የህብረተሰቡን ችግር ፈች የሆኑ ምርምሮች በጋራ ለማካሄድ እንደሆነ ገልፀዋል።

በተጨማሪ በጋልማ አማካኝነት እየተመሠረተ ከሚገኘው ሰላም ማይክሮ ፋይናንስ በመጀመሪያ ዙር 20 አክሲዮኖችን 100ሺ ብር ለመግዛት፣ የኮሌጁን ሠራተኞች መምህራንና ተማሪዎችን የልማት ማህበሩ አባል ለማድረግና ኮሌጁም የማህበሩ የሲልቨር ደረጃ አባል ለመሆንና ሌሎችም ስምምነቶች ለመፈፀም የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

በልማት ማህበሩ በኩልም ለኮሌጁ ተማሪዎችና መምህራን የኢንተርንሺፕና የኤክስተርንሺፕ አገልግሎት ለመስጠት፣በልማት ማህበሩ የእንሰሳት እርባታና ድለባ፣በአዝርዕትና ፍራፍሬ ልማቶች በግብርናው ዘርፍ የሚሠለጥኑ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ ለማድረግ፣የሳታ የላቀ ውጤት ተመራቂዎችን ተቀብሎ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና በሌሎችም መስኮች በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን አቶ ባዩ አብራርተዋል፡፡

የስምምነት መርሃ ግብሩ ኮሌጁ አዲስ በማስገንባት ላይ ባለው የራሱ ህንፃ ጋሮ ካምፓስ ውስጥ በጋሞ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሆኑት በዶ/ር ደምስ አድማሱና በሳታ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ ዲን በአቶ ዓለማየሁ ካሳ መካከል መከናወኑ ታውቋል።

ሳታ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ ከ14 ዓመታት በላይ ያስቆጠረና በከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ የተሠማራ አንጋፋ የትም/ ተቋም ሲሆን በተለያዩ የእድገት ደረጃዎችና የሥልጠና መስኮች የመጣ የግል ተቋም ነው።

ኮሌጁ ከአጫጭርና የቴክኒካና ሙያ ስልጠናዎች

ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ከ10ሺ የማያንሱ ተማሪዎችን በአርባምንጭ፣ በሳውላና ጂንካ ካምፓሶች አስመርቆ ያሰማራና በርካታ ተማሪዎችንም በማሰልጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን ነፃ በአቅም ምክንያት መማር ያልቻሉና የከፍተኛ ትምህርት ውጤት ላመጡ ነፃ የትምህርት እድል ከመስጠት ጀምሮ ለአካባቢውና ለሀገር ልማት ግንባር ቀደም በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።

የመንግስትን ፖሊሲ አቅጣጫ በመከተል የሥልጠና አድማሱንና ተደራሽነቱን በማስፋት ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለማደግ ራዕይ አስቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝ ኮሌጁ አስታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Posts