አርባምንጭ፡ሚያዚያ 5/2016 ዓ/ም (አርባምንጭ ከተማ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን)
በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሲያራ ባስኑር አርባምንጭ ላይ ሳታ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ በመገኘት ዋና ግቢውንና ጋሮ ካምፓስ ያለውን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ጎበኙ።
ሳታ ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በጋሞ ዞን እና አከባቢው ብቁ የሰለጠነ የሰው ሀይል ሲያቀርብ መቆየቱን አውስተው ከትምህርት ዘርፉ ባሻገር በበርካታ የልማት ስራዎች እየተሳተፈ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች አጫጭር ስልጠና፣ ነፃ የትምህርት እድል በመስጠት እና በበጎ አድራጎት ስራዎች እየተሳተፈ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አለማየሁ ለበርካታ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሯል ብለዋል።
ኮሌጁ በቴክኒክና ሙያ፣ በድግሪ እና በማስተርስ መረሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በ6 ካምፓሶች ከ7 ሺህ በላይ ሠልጣኞች እያስተማረ እንደሚገኝ ዲኑ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሲያራ ባስኑር በጉብኝቱ ወቅት በኮሌጁ የተከናወኑና እየተከናወነ ያለው ነገር እጅግ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።
በኢንዶኔዥያ ውስጥ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን ላይ በመምህርነት ማገልገሉን የገለጹት አምባሳደሩ ሳታ ቢዝነስ ኮሌጅ በመማር ማስተማር ዘርፍ ላይ እየሠራ ያለው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ በኢንዶኔዥያ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ገልጸው አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
አከባቢው ለግብርና ሥራ ምቹ እንደሆነና በርካታ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ እንደሚቻል ገልጸው ቀጣይ በትኩረት ሊሰራ ይገበዋል ብለዋል።
በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የእንቦጭ አረም የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በጋራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
አቶ ደረጀ ጳውሎስ የአርባምንጭ ከተማ ዋና የመንግሥት ተጠሪ አርባምንጭ ከተማን ከትላልቅ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ለነዋሪዎች፣ለእንግዶችና ለቱሪዝም ተመራጭ እንዲትሆን ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው የኢንዶኔዥያ አምባሳደር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።
ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ከተማዋን ለማሳደግ በጋራ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኮሌጁ ዲን አቶ አለማየሁ ካሣን ጨምሮ የአርባምንጭ ከተማ ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ደረጀ ጳውሎስ፣የኮሌጁ አካዳሚክና አስተዳደር አመራሮችና ሌሎችም ተገኝተዋል።
በመጨረሻም ኮሌጁ በሸማ ፓርክ የተዘጋጀ የጋሞ ባህልን የሚገልጽ ቡሉኮ ስጦታ ለአምባሳደሩ አበርክተዋል።




